የህይወት መንገዴ
- snigussie
- Feb 10, 2022
- 1 min read
እንደ ብዙሃኑ ወልጄ ከብጄ
የተፈጥሮን ጥሪ አድምጬ ፈቅጄ
አልኖርኩም በወጉ ኑሮዬን አቅጄ
ይልቅ እጓዛለሁ በቀለም ሰክሬ
ሱስ ሆኖብኝ እውቀት ይኳትናል እግሬ
እጆቼ ይደክማሉ ይናውዛል ቀልቤ
ይሰደዳል ልቤ ይዋኛል ሀሳቤ
በጥበብ መዓዛ ወደፊት ተስቤ
ስምግ አረፍዳለሁ ከብራና ከርቤ
እውላለሁ ሳስስ ስነጠቅ ወደላይ
ክንፍ አውጥቼ ስበር በደመና ሰማይ
ስፈትሽ የኖርኩት የዘመናት ቅኔ
በጥልቅ ትንታኔ በሀሳብ ምናኔ
በስጋ ድካሜ ለነፍሴ ስንቅ ሀሴት
ለህሊና እርካታ ለመንገዴ ስምረት
አንዳች ባገኝ ብዬ የሚያፀና ሕይወት
አልፎ ሂያጅ ደስታን የሚያዘልቅ በረከት
እድሜ እማይገድበው የማያረጅ እውነት
ቀለሙ የማይለቅ ደብዝዞ እማይጠፋ
ከነፍስ የሚዋደድ ሰፍሬ በጭልፋ
ከጠቢባን ባህር ጥቂት ከፈላስፋ
ለማቅናት ነው መንገድ የሚበጅን ተስፋ
Comments